ዩኒቨርሲቲው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረጋቸው የሚገኙ ጥረቶች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው

ዩኒቨርሲቲው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረጋቸው የሚገኙ ጥረቶች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው

====

ሮቤ ህዳር 23/2018(ኢዜአ) የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እያደረጋቸው የሚገኙ ጥረቶች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸው ተመለከተ።

ዩኒቨርሲቲው ‘የስንዴ ምርታማነታችን ለግብርናችን እምርታ”በሚል መሪ ሀሳብ በዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያ እና የአርሶ አደሮች ኩታገጠም የስንዴ ማሳ የባለድርሻ አካላት የመስክ ቀን ምልከታ አካሂዷል።

ዩኒቨርሲቲው እያካሄዳቸው የሚገኙ ምርምሮች በተለይ በስንዴ ሰብል ምርምር የልህቀት ማዕከል ለመሆን ላስቀመጠው ግብ አጋዥ መሆኑም ተመላክቷል።

በመስክ ምልከታው ላይ ከተሳተፉት ባለድርሻ አካላት መካከል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኦቱከና ኦዳ (ዶ/ር) እንዳሉት የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል።

የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና የሥራ ዕድል ምንጭ መሆንን ጨምሮ ሌሎች ዋና ዋና ግቦችን እንዲያሳካ የተቀረጹ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መጀመራቸውን በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በተለይ የግብርና ምርምር መዕከላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቀናጀት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ይበልጥ የሚያሻሽሉና በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በምርምር እንዲፈቱ እያደረጉት የሚገኘው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው ብሏል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ ሂደት በተጓዳኝ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እያደረጋቸው የሚገኙ ተግባራት በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውንም አመልክተዋል ።

በክልሉ በመኽር የምርት ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች ከለማው ከ10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ386 ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሂርጳ ናቸው።

መንግስት አርሶ አደሩ ከዘልማዳዊ የግብርና አሰራር ተላቆ በመካናይዜሽን የተደገፋ የኩታ ገጠም ግብርና አሰራሮች እንዲሸጋገር እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ እንደሚሆን በባሌ የተለያዩ ወረዳዎች ባደረጉት የመስክ ምልከታ መታዘባቸውን አንስተዋል።

በተለይ መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት የሰብል በሽታዎችን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የስንዴ ዝርያዎች ላይ እያካሄዳቸው ያሉ የምርምር ሥራዎች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን በመስክ ምልከታው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ በበኩላቸው፤ በዞኑ በመኽሩ ወቅት ከ528ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች እየለማ ነው።

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን አርሶ አደር በሚያካሄደው ምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግርዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ተግባር በተጓዳኝ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የግብዓት አቅርቦትና ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ ነው።

በተለይ ዩኒቨርሲቲው በስንዴ ሰብል ላይ ሰፊ የምርምር ስራዎችን በራሱና በአርሶ አደሩ የእርሻ ማሳ ላይ በማካሄድ በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ ምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ብርሀነመስቀል እንዳሉት፣ ዩኒሸርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት በባሌ፣ ምሥራቅ ባሌ እና በምዕራብ አርሲ በኩታ ገጠም እርሻ ለተደራጁ የተመረጡ አርሶ አደሮች ባደረገው ሙያዊና የግብርና ግብዓት ድጋፍ በምርታማነት ላይ ለውጥ እየታየ መጥቷል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይ በአርሶ አደሩ አቅራቢያ የከፈታቸው የምርምር ጣቢያዎች አርሶ አደሩን ከተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ጋር ይበልጥ እንዲላመዱ እያገዙ በመሆናቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው በተደረገላቸው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፍ በመጠቀም ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር ስንዴን በኩታገጠም እያለሙ የሚገኙ የሲናና እና አጋርፋ ወረዳ አርሶ አደሮች ከልማቱ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት በተካሄደው የመስክ ምልከታ ላይ ተመራማሪዎች፣አርሶ አደሮችና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ኢዜአ ፣