የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሀብት ልማትና ገቢ ማመንጫ የዩኒቨርሲውን ገቢ ለማሳደግ እና ሀብት ለማፍራት ተጠናክሮ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
**************************************
(ባሌ-ሮቤ ህዳር 16/2018 ዓ.ም መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሕ.ዓ.ግ.ጽ)
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የተከበሩ ዶ/ር ብርሀነመስቀል ጠና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሰጣቸውን ተልእኮ ለማሳካት የራሳቸውን ገቢ ማመንጨትና ሀብት ማፍራት ግዴታ በመሆኑ የኛም ዩኒቨርሲቲ ያለውን ሀብትና የሰው ሃይል በመጠቀም ከበፊቱ በተሻለ መልኩ መስራት እንዳለበት አሳሰቡ፡፡
የዩኒቨርሲውን ገቢ ለማሳደግ እና ሀብት ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር እና ልማት ምከትል ፕሬዝዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ኢሳ ሀሰን ናቸው፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን እንዲችሉና የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል ተጠናክሮ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ በልማትና ሀብት ገቢ ማመንጫ ስራ አስፈጻሚ ስር ከሚንቀሳቀሱ እና የሀብት ማፍራት ማፈላለግ የስራ ዘርፍ መካከል አንዱ የሀብት ልማትና ገቢ ማመንጫ ቡድን ነው ብለው፤ በ2018 ዓ.ም በጽ/ቤቱ ስር ከሚከናወኑና በርካታ የልማት ስራዎች ውስጥ የድለባ በሬዎችን ገዝቶ በማደለብ በተሸለ ዋጋ ለመሸጥ ማቀዱን ተናግረዋል፡፡
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሀብት ልማት እና ገቢ ማመንጫ ጽ/ቤት ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት አቲካ አህመድ በ2018ዓ.ም የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ እና ሀብት ለማፍራት የሥጋ በሬዎች ድለባ፣በአትክልትና ፍራፍሬ ሌሎችንም በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ወ/ሪት አቲካ አክላም ጽ/ቤቱ በዚህ በሁለተኛው ሩብ ዓመት ለበሬ ግዢ በዩኒቨርሲቲው በተቋቋመው ኮሚቴ እስከ አሁን ድረስ 61 (ስልሳ አንድ) ለማደለብ የሚሆኑ በሬዎችን ከመልዩና ሮቤ ገበያዎች በመግዛት እየተንከባከበ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በርካታ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንደ ጥቅል ጎመን፣ቀይ ሥር፣ካሮት፣ድንች፣አበባ ጎመን እና ሌሎችንም በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከማቅረብ አልፎ ወደ ገበያ በመውሰድ የውስጥ ገቢውን እያሳደገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይነትም በጎባ ሪፈራር ሆስፒታል የትሪትመንት ፕላንት አጠገብ ያለውን 1.5 ሄክታር መሬት ለእርሻ ስራ እንዲውል የመስክ ምልከታ ጥናትና ለማልማት ዝግጅት መጀመሩ ታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይነትም ከግብርና እንዲሁም ከሆቴልና ቱሪዝም ጋር በተያያዘ በርካታ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሊያከናውን ማቀዱን ካገኘነው መረጃ መረዳት ይቻላል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ብርሀነመስቀል ጠና በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች እንደሚያነሱት ዩኒቨርሲቲውን ተወዳዳሪና በደንበኞቹ ተፈላጊ ለማድረግ የመማር ማስተማር፣ጥናትና ምርምርን፣የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሳደግና የሰራተኞችን ሁለንተናዊ የመፈፀም ብቃት ለማረጋገጥ ብሎም የዩኒቨርሲቲውን የወደፊት የራስ ገዝነት ጉዞ ለማሳለጥ የውስጥ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ በተጨማሪም እነዚህን ወሳኝ የልማት ስራዎች ከግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ስር ከእንስሳት ሳይንስ (Animal & Range Science) እና የእፅዋት ሳይንስ (Plant Science) ትምህርት ክፍሎች ጋር በማስተሳሰር የተግባር ት/ት ከመስጠት ባሻገር ስራውን የበለጠ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ማሳደግ እንደሚቻል በሚገባ ያብራራሉ፡፡
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጽ/ቤት










