የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ከፈረንሳይ የሐኪሞች ቡድን ጋር በመተባበር የሀሞት ጠጠር የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጠ::

የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ከፈረንሳይ የሐኪሞች ቡድን ጋር በመተባበር የሀሞት ጠጠር የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጠ::
=======
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል “ሜድሰርጅ ሰፖርት” የተሰኘ የፈረንሳይ ግብረ ሰናይ የሐኪሞች ቡድን ጋር በመተባበር ለ26 ታማሚዎች የሀሞት ጠጠር የቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጠ።
ግብረሰናይ ድርጅቱ ለህሙማን ከሰጠው ነፃ የህክምና አገልግሎቱ በተጓዳኝ ለህክምና የሚውሉ ዘመናዊ ማሽኖች ድጋፍና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና መስጠቱም ተመልክቷል።
በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ከበበ በቀለ፣ የሀሞት ጠጠር ቀዶ ህክምናውን ከሰጡ የሐኪሞች ቡድን ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸዋል።
“ላፓረስኮፒ” በሚባል ዘመናዊ የህክምና መሳሪያ የሚሰጠው ይህ የቀዶ ህክምና ዓለም የደረሰበት ጥራት ያለው የህክምና እንደሆነ ጠቁመዋል።
“የህክምና አገልግሎቱ ዘመናዊ በመሆኑ ታካሚው በቶሎ አገግሞ ወደ ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ ከማስቻል ባለፈ የእውቀትና የግብዓት ሽግግር የተደረገበት ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም ህክምናው በታካሚው ሰውነት ላይ አነስተኛ ጠባሳ ብቻ የሚያስቀርና የቀዶ ህክምናውን ሥራ የሚያቃልል እንደሆነ አስረድተዋል።
ዶክተር ከበበ እንዳሉት፣ ከቀዶ ህክምናው ባለፈ 4 ለህክምናና ለተማሪዎች መለማመጃ የሚሆን ‘የላፓራስኮፒ’ ማሽን፣ 3 የታማሚ መከታተያ ማሽንና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች በድጋፍ ተገኝቷል።
የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም፤ ሆስፒታሉ መሠረታዊ የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እያደረገ ነው ብለዋል።
ሪፈራል ሆስፒታሉ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ይበልጥ ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ ግንባታን የማስፋፋትና አዳዲስ ህክምናዎችን ለመጀመር የሚያግዙ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በሆስፒታሉ በአዲስ መልኩ ለመጀመር ከታቀዱት ህክምናዎች መካከል የ’ኤም.አር.አይ’፣ ‘ሲቲስካን’፣ የምግብ መውረጃ ቱቦና የጨጓራ ካንሰር ህክምና፣ የእንዶስኮፒ ምርመራና የህክምና ይገኝበታል ነው ያሉት።
ሪፈራል ሆስፒታሉ ከፈረንሳይ የኃኪሞች ቡድን ጋር በመቀናጀት በኃሞት ጠጠር ላይ ያደረገው የህክምና አገልግሎትና ሥልጠና የዚሁ ጥረት ማሳያና ቀጣይነት የሚኖረው እንደሆነም አመልክተዋል።
በተለይ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ በሆስፒታል አቅም የማይሞከር ከመሆኑም ባሻገር ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሳካ ህክምና ለመስጠት ሚያስችል በመሆኑ ድርጅቱን አመስግነዋል።
የ”ሜድሰርጅ ሰፖርት” ግብረ ሰናይ ድርጅት ኃላፊና የኃክሞች ቡድን አባል ዶክተር ማሪያ ሲስሊ በበኩላቸው፣ “ወደ ጎባ መጥተን ማገልገልና ልምድ ማካፈል በመቻላችን ደስተኞች ነን” ብለዋል።
በቀጣይም ትብብሩን በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና አገልግሎት የተደረገላቸው ወይዘሮ መሠረት ከበደ፤ለረጅም ዓመታት በሀሞት ጠጠር ህመም ሲቸገሩ እንደነበር ገልጸው “ህመሙ ሲጠናብኝ መጥቼ የተሳካ ህክምና አግኝቻለሁ” ብለዋል።
ሌላዋ ታካሚ ወይዘሮ አስቴር ከተማ፣ በሆዳቸው አካባቢ በተከሰተ ህመም ጤና አጥተው ለችግር ተዳርገው እንደቆዩ ተናግረዋል።
ተመርምረው የሀሞት ጠጠር ታማሚ መሆናቸውን አውቀው በተመቻቸው የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በየዓመት የሁለቱ የባሌ ዞኖችን ጨምሮ ከሌሎች አጎራባች ዞኖች የሚመጡ ከ250 ሺህ ለሚበልጡ ህሙማኖች የህክምና አገልግሎት እየሰጥ መሆኑን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
+6