Madda Walabu University crest
Madda Walabu
University · Est. 2005
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከግንባታ አማካሪ ድርጅቶች ጋር የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ ።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከግንባታ አማካሪ ድርጅቶች ጋር የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግምገማ አካሄደ ።

Jun 17, 2026

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በዋናው ካምፓስ፣ በጎባ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና በሻሸመኔ ካምፓስ በመካሄድ ላይ ያሉ የግንባታ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ለመገምገም ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር ሰፊ የግምገማ መድረክ አካሄዷል። በግምገማው የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ያሉበት አሁናዊ ደረጃ፣ የተጋረጡ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች በዝርዝር ተዳሰዋል።

ግምገማውን የመሩት የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተቱ የቆዩ የግንባታ አማካሪ ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን በልዩ ትኩረት እና ቀጣይነት ባለው ድጋፍ፣ ክትትልና ግምገማ በማድረግ እንዲፋጠኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው፤ በተለይም ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት፣ ለምርምር፣ ለማህበረሰብ አገልግሎት እና ለጤና አገልግሎት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


በግምገማ መድረኩ ላይ በዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወኑ የሚገኙ ሁሉም የአማካሪ ድርጅቶች ተገኝተው የፕሮጀክቶቻቸውን ወቅታዊ ሁኔታ በሪፖርት አቅርበዋል። በሪፖርቶቻቸውም የግንባታ ሂደቶች የደረሱበትን ደረጃ፣ የቀሩ ስራዎችን፣ የቁሳቁስ አቅርቦት ሁኔታን እና የፕሮጀክቶቹን ማጠናቀቂያ ጊዜ ሰሌዳ በዝርዝር አብራርተዋል።

እየተገነቡ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል ቤተ-መጻሕፍት፣ የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾች፣ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ማስፋፊያ ሕንፃ፣ የምረቃ አዳራሽ፣ የተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃዎች እና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ይገኙበታል። 


በመድረኩ ላይ የተገኙ አማካሪ ድርጅቶች በበኩላቸው በየጊዜው እየጨመረ ያለው የገበያ ዋጋ ለፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ ተግዳሮት መፍጠሩን ገልጸው፤ ይሁን እንጂ ግንባታዎቹን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለማጠናቀቅ የተቀናጀና የማያቋርጥ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ 

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳ ሐሰን በበኩላቸው፣ በቅርብ ጊዜያት በፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሂደት ላይ የተጨበጠ እና አበረታች ለውጥ መታየቱን ጠቅሰው፣ ይህ እንቅስቃሴ በሁሉም ተቋራጮች በተመሳሳይ ቁርጠኝነት እና በበለጠ ፍጥነት ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል። 


በማጠቃለያው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃነመስቀል ጠና፣ የተቋሙን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ የተጀመሩ ሁሉም ግንባታዎች በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆን እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተው፤ የሪፎርም ሂደቱን ተከትሎቆመው የነበሩ ፕሮጀክቶች ወደሥራ በመመለስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየው የስራ እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም፣ አማካሪ ድርጅቶች ውልን የማስተዳደር እና ጥራትን ዋነኛ መርህ አድርገው በበለጠ ፍጥነት እንዲሰሩ አሳስበው፣ ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለተማሪዎችና ለማህበረሰቡ አገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ፤ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና በቀጣይም የተጠናከረ ክትትልና ግምገማ እንደሚካሄድ አስገንዝበዋል።


Related Articles

View All