በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ 9 ኛው አመታዊ የጥናትና ምርምር ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ጉባኤው ከሰኔ 22-ሰኔ 23/2014 ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚዘልቅ ይሆናል፡፡ በጉባኤው በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የተደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚገመገሙበት እንደሆነም ተገልፅዋል፡፡ በነዚህ በሁለት ቀናት ቆይታ ሰባሰባት/77/ የሚደርሱ በተለያየ ዘርፍ የተከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው የሚገመገሙ ይሆናል፡፡
በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዘደንት ዶ/ር ሀሰን ሽፋ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በኋላ እንደገለፁት መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ በመግለፅ የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት አቅጣጫ እና ተልዕኮ ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ በግብርና፣በተፈጥሮ ሀብት እና ቱሪዝም ዙሪያ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ዩኒቨርሲቲው ሜጋ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በአንድ ዓመት የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ፕሮጀክቶች በሚቀረፁ ወቅት የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት አቅጣጫ እና ተልዕኮ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባም ለተመራማሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘደንት ተወካይና የአካዳሚክ ጉዳይ ምክትል ፕሬዘደንት ዶ/ር በዛብህ ወንድሙ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው እንተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር በጥናትና ምርምር በማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ብርካታ ተግባራት እያከናወን ያለ ተቋም እንደሆን ገልጸው በተለይ በጥናትና ምርምሩ ረገድ ስንመለከት የዛሬውን ጉባዔ ልዩ የሚያደርገው ዛሬ ላይ የሚቀርቡት የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደከዚህ በፊቱ ከሌሎች ተቋማት በሚጋበዙ ተመራማሪዎች ሳይሆን በተቋሙ ተመራማሪዎች የሚቀርቡ መሆናቸው ጉባዔውን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል ፡፡
በጉባኤው የሀገር ሽማግሌዎች፣አባ ገደዎች፣ ሀደ ሲቄዎች እና ከሶስት ዞኖች የመጡ ባለድርሻ አካላት በጉባዔው ተሳታፊዎች የሚሆኑ ይሆናል፡፡