የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባላት ከዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሄዱ! መስከረም 08/2015

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባላት ከዩኒቨርሲቲው መምህራን/Academic staffs/ እና ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ዶ/ር በለጠ ሞላ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው እንደ ሀገር የተሰጠውን ተልዕኮ ማስፈጸም ይችል ዘንድ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ፣ አስተዳደር ሰራተኞች ፣ አካባቢው ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ተቋሙ የተሰጠውን ተልእኮ ከግቡ እንዲደርስ ያስችለዋል ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ግዙፍ እና ሀገራዊ ተቋም እንደመሆኑ በተቋሙ ጥላ ስር የተሰባሰቡ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ መቻሉ ያሉ ችግሮችን በማንሳት እና ውይይት በማድረግ ተቋሙ በቀጣይ ለሚኖረው እመርታ ትልቅ ግብአት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጋራ ጥረት ችግሮችን መፍታት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር በላይ ስማአኒ በበኩላቸው መምህራን ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር ያላቸው ሀላፊነትና አስተዋጽኦ በርካታ በመሆኑ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ረገድ የነበራቸውን እና ወደፊት ሊኖራቸው ስለሚገቡ አበርክቶዎች በውይይቱ ሊነሱ የሚገባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ አመላክተዋል። ሌላኛው የስራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አንተነህ ተስፋዬ በበኩላቸው በዪኒቨርሲቲው የተያያዘው የለውጥ መንገድ አመራሩና ሠራተኞቸው እየተደጋገፉ ከቀጠለ በአጭር ጌዜ ውስጥ የተሻለ ውጤት ማሳየት እንደሚችል ጠቁመዋል ።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በተቋሙ ያለውን ጠንካራ ጎኖች እና ውስንነቶችን አንስተው በትኩረት ሊሠሩባቸው ይገባል ያሉትን ጉዳዮች ለቦርዱ አስረድተዋል ። በመጨረሻም የቦርዱ አባላት ከመምህራን እና ሠራተኞች በተነሱት ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር ተወያይቶ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቋል ። እንዲሁም የቦርዱ አባላት የተለያዩ በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል ።
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ
ባሌ ሮቤ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

X